የምስራቅ ጉራጌ ዞን መንግስት ከሚኒኬሽን መምሪያ ከዞኑ ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መምሪያ ጋር በመተባበር ያለማው ዌብሳይት ርክክብና ይፋዊ የአገልግሎት ማስጀመሪያ ፕሮግራም ተደረገ።
መጋቢት 17/2018 ዓ.ም (ቡታጅራ)
በትብብር የበለፀገው የዞኑ መንግስት ኮሚኒኬሽን ዌብሳይት ዞናዊ የመረጃ ማግኛ ቋት ሆኖ አገልገሎት መስጠት መጀመሩን በይፋ ተበስሯል።
የምስራቅ ጉራጌ ዞን መንግስት ኮሚኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ ካሳሁን ቱጂ በዌብሳይት የሶርስ ኮድ ርክክብና ይፋዊ የአገልግሎት ማስጀመሪያ ፕሮግራሙ ላይ እንደተናገሩት ዌብሳይቱ የኮሚኒኬሽን መምሪያው ካሉት ፕላትፎርሞች በተጨማሪ የዲጂታል መረጃ አያያዝና ተደራሽነታችን ከፍ የሚያደርግ ሁሉንም መረጃዎች በአንድ ማዕከል ማግኘት የሚያስችል ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያለው ነው ብለዋል።
ይህን ዌብሳይት በዞኑ በማህበራዊ በኢኮኖሚያዊና በፖለቲካዊ ዘርፎች የሚከናወኑ ሁነቶች በተደራጀና በተቀናጀ መልኩ ለማስቀመጥ መረጃ ፈላጊውም በቀላሉ ሰርች በማድረግ የሚያገኝበት በዞኑ ያሉ የተፈጥሮና ሠው ሠራሽ ፀጋዎች ለማስተዋወቅና ለመሸጥም የሚያግዝ ሁነኛ የመረጃ ምንጭ እንደሆነ አስረድተዋል።
አክለውም አቶ ካሳሁን ዌብሳይቱን/ድረ-ገፁን/ ለማልማት የተለያዩ ህጋዊና ሙያዊ የቴክኒክ ሂደቶችን አልፎ ለአገልግሎት በመብቃቱ መደሰታቸውን በመግለፅ በሂደቱ ሚና ለነበራቸው የሳይንስና ቴክኖሎጂ መምሪያ አመራርና የዘርፉ ባለሙያዎች ላደረጉት ጥረት አመስግነዋል።
የምስራቅ ጉራጌ ዞን ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ልክየለሽ ከበደ በበኩላቸው በርክክቡ ወቅት እንዳሉት ልምቶ ወደ ሥራ የገባው የዌብሳይት ቴክኖሎጂ የኮሚኒኬሽን ተቋሙ የሚያሰራጫቸው አዳዲስ ዞናዊ መረጃዎች አማራጭ መገኛ ከመሆኑ ባሻገር ዞናችን ያሏት የተለያዩ ሀብቶች ለማስተዋወቅና ለመሸጥ የሚያስችል እንደሆነ ገልፀዋል።
ዌብሳይቱ በመስሪያቤታቸው ባለሙያዎች እውቀትና ጥረት የለማ መሆኑን በመጠቆም በቀጣይም በማስተዳደርና በመረጃ አደረጃጀት ላይ የሚያስፈልጉት ሙያዊ ስልጠና ለመስጠት እንደመምሪያ ያላቸውን ዝግጁነት ገልፀዋል።
በበለፀገው ድረ-ገፅ የመረጃ የመለቀቅና አስተዳደር የአልጎሪዝም ባህሪና የካታጎሪ ጉዳዮች ላይ በዞኑ ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መምሪያ የዘርፉ ኤክስፐርቶች አማካይነት ገለፃና ማብራሪያ ተሰጥቷል።
በመጨረሻም በሁለቱ የዞኑ መምሪያ ኃላፊዎች መካከል የዌብሳይት ሶርስ ኮድ ርክክብ በማድረግ የዕለቱ ፕሮግራም ተጠናቋል።
ዘገባው የምስራቅ ጉራጌ ዞን መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።

